Thursday, July 11, 2013

 Posted by Mwsfin Tadese 

July 11,2013

ጉዱ የማን ሆነና?

ከግርማ ታደሰ
ይድረስ ለአቤ ቶክቻው
ይህን ደብዳቤ በቅርቡ “ጉድ በል ሰላሌ” በሚል ርእስ ባወጣኸው ላይ ተመርኩዤ የፃፍኩት ሲሆን እሱን በአንድ ቁምነገር በመያዜ ምክንያት ሳላወጣው ብቆይ ሌላ ጦርነት በኦሮሞና በተለይም ጃዋር ላይ ስትከፍቱ (አንድ ታዛቢ “ጨርቅ ጥሎ ማበድ” ብሎታል)በግርምት እየተከታተልኩ ቆየሁ::
ለነገሩ ለእንቶ ፈንቶ መልስ እየሰጡ እሰጥ አገባ መግጠምና ጊዜ ማጥፋት አስፈላጊ ባይሆንም እንቶ ፈንቶ ሲበዛ እውነት የሚመስላቸው ስለማይጠፉ መልስ መስጠት የግድ ይላል::
አንዳንድ ነጥቦችን ላንሳና ወደ ዋናው መልዕክት እሄዳለሁ::
1) ከሰሞኑ በግብፅ UNHCR ፊት ለፊት ሲካሄድ የነበረው የድረሱልን ጥሪ አሁንም እንደ ቀጠለ ነው፤ ይሁንና ከኦሮሞ፣ከግብፅና ከአልጀዚራ ድረ-ገፆች ውጭ ሲዘገብ አይታይም:: እርግጥ አንተና መሰሎችህ እንደ ዜና ሳይሆን ሰላማዊ ሰልፈኞቹን ለማጥቃት አንድ ሰሞን አንስታችሁታል:: እሱን ወደ ኋላ እመለስበታለሁ::
2) አንተም ሆንክ መሰል ዘላፊዎች ትኩረታችሁን ያደረጋችሁት በመጀመሪያ ቀን ካነገቧቸው ወደ አስር የሚጠጉ መፈክሮች ውስጥ “ኦሮሞዎች እንጂ ኢትዮጵያውያን አይደለንም” የሚለው ላይ ነው:: ስለአንኳር ጥያቄያቸው ሲጀመርም ደንታም የላችሁ፤ ከዚያ በኋላ የት እንደደረሱ የማወቅ ፍላጎትም የላችሁ:: አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎችማ ስደተኞቹ ተሰብስበው እስር ቤት ቢታጎሩ ደስ ይላቸዋል::
3) ይሄ “ኢትዮጵያዊነትን አለመቀበል” አስተሳሰብ በ”ኢትዮጵያ አንድነት አማኞች” ዘንድ እጅግ የሚብጠለጠል ቢሆንም አሁን የመጣ ወይንም አዲስ ክስተት አይደለም:: ኦሮሞዎች ብቻ ሳይሆኑ የኦጋዴን ተወላጆች፣የሲዳማ ብሄርተኞችና ሌሎችም ይሄን አስተሳሰብና እምነት ያራምዳሉ፤ ይህም የራሱ የሆኑ የተለያዩ ምክንያቶች አሉት:: ሰሞኑን ጨርቅ ያስጣላችሁ ዕብደት አደባባይ ሲወጣማ መሃል ሲያንዣብብ የነበረው ሳይቀር ሁሉም በየፊናው “ይሄስ ኢትዮጵያዊነት በአፍንጫዬ ይውጣ – መጀመሪያ (ብሄሩን እየጠቀሰ) ሲዳማ ነኝ ወዘተ” ማለቱን ቀጥሏል::
4)በአንፃሩደግሞ እነዚህን ወገኖች “ኢትዮጵያውያን አይደሉም” የሚሉ “ንፁህ ኢትዮጵያውን”ም አሉ:: ይሄንን አይነት “ኢትዮጵያዊነት” ደግሞ አገሪቱን የሚያስተዳድሩት ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ሳይቀሩ በጥብቅ የሚጠየፉት እንደሆነ በአንድ ወቅት ቃለምልልስ ላይ ተናግረዋል:: የኢትዮጵያው መሪ የሚዘልፉትን ዓይነት “ኢትዮጵያዊነት” የኢትዮጵያ መንግስት ግፍ ሰለባ የሆኑት አንቀበልም ቢሉ ምኑ ላይ ነው ድንቁ?
እሩቅ ሳንሄድ በ2012 መባቻ ላይ ቀጣሪ ጌቶችህ የ”ዓመቱ ምርጥ ኢትዮጵያዊ” ብለው አበበ ገላውን ሲሸልሙ በዚያው ዓመት እነ ጥሩነሽ ዲባባ በኦሎምፒክ ዓለምን ሲያስደምሙ ነበር:: ታዲያ እነዚህን ኦሮሞች እንደ “ኢትዮጵያዊ” ሳትቆጥሩ ኦሮሞው “ኢትዮጵያዊ”ነቱን ከጥያቄ ሲያስገባ “እኛ የምንተገብረውን ተረድተው ነው” አትሉም ነበር? ነው ወይንስ አበበ ገላው የቀድሞውን ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊን ተሳድቦ የ”ዓመቱ ምርጥ ኢትዮጵያዊ”ን “ክብር” ስለተጎናፀፈ አንተም ኦሮሞችን ተሳድበህ ልትሸለምበት አቅደህ ነው? እቅድህ ባልከፋ ነበር፤ ነገር ግን ኦሮሞነትህን እንደደበቅከው ብትቆይ ያዋጣህ ነበርና ተስፋ ያለህ አይመስለኝም:: በነገራችን ላይ መለስ ዜናዊን አምርሬ ብቃወምም አበበ ገላው እና አንተ እድሜ ልካችሁን የማትሰሩትን አምባገነኑ ሰው ባንድ ወር እንደሚሰሩ ጥርጥር የለኝም:: ሌላው ቢቀር ይሄን ጣጠኛ ግድብ ያስጀመሩት ሰውዬው ናቸው::
5)የኦሮሞን ጥያቄ ለማጥላላትና ለማሳነስ ልክ አንተ እንዳልከው “የተጨቆኑት ኦሮሞዎች ብቻ ናቸው እንዴ” የምትለዋ በጣም የተለመደች ናት:: ይሄ እውነት ነው፤ ኦሮሞዎች ብቻ ሳይሆኑ ሌሎች በርካታ ብሄሮች ለዘመናት በአምባገኖችና በጨቋኝ ተስፋፊዎች ሲበዘበዙ፣ሲዋረዱና በባርነት ሲሸጡ እንደነደነበር ዛሬም እንዳሉ የታወቀ ነው:: የኦሮሞ ፖለቲካ ድርጅቶች በሙሉ ይሄንን ይገነዘባሉ፤ መቸም እኛ ብቻ ነን ተበዳይ ብለው አያውቁም:: ጥያቄው ማተኮር ያለበት ግን ኦሮሞ ላይ የሚደርሰው ግፍ እንዴትና ለምን ተለየ የሚለው ላይ ነው:: ለዚህ ደግሞ ምስክርነት የሰጡት በኦሮሞ ህዝብ ወዳጅነታቸው የማይታወቁት ስዬ አብርሃና ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ናቸው:: ሁለቱም በእስር ቤት በነበሩበት ወቅት ያስተዋሉትን ሲገልፁ እስር ቤቱ ውስጥ ኦሮሞ ከመብዛቱ የተነሳ “የእስር ቤቱ ቋንቋ ኦሮምኛ/አፋን ኦሮሞ ነው” ብለዋል:: አንዳንድ ጥናታዊ ግምቶች የኦሮሞ ፖለቲካ እስረኛ እስከ 95% ይደርሳ ል ይላሉ:: የአደባባይ ምስጢር የሆኑትን ሌላ ሌላውን ሳንጨምር ይሄ ብቻውን በኦሮሞ ላይ በተለየ የሚደርሰውን ግፍ ባመላከተ ነበር::

source: http://ayyaantuu.com

No comments:

Post a Comment